ያደመቀን መብራት ሲደበዝዝ

ያደመቀን መብራት ሲደበዝዝ መልካችን ምን ይመስላል?

(መዝሙር 131፡1- 3)

ዳዊት ገና የአባቱን በጎች ሲጠብቅ ሳለ አንበሳና ድብ እየመታ በጎቹን ያስጥል ነበር። ከወንድሞቹም መካከል ተመርጦ ለንግሥና በሳሙኤል ተቀባ ። በሙዚቃ ችሎታ ተወዳዳሪ አልተገኘለትምና ንጉሱን እንዲያፅናና ተጠራ።እስራኤልን የተገዳደረውንና በእግዚአብሄር ስም ላይ የተሳለቀውን ጎልያድን ገድሎ እስራኤልን ታደገ። ሳዖል ሺህ ገደለ ዳዊት እልፍ ገደለ እያሉ ሴቶች እየተቀባበሉ ዘፈኑለት። የእስራኤልን ጭፍራ እየመራ ብዙ ጊዜ ድል ያደርግ ነበር። በሳዖል ይፈራ ፤ በልጁ በዮናታን እጅግ ይወደድ ነበር። በእስራኤል ሁሉ የተወደደና በሁሉ ፊት ሲገባና ሲወጣ አስተውሎ ያደርግ ነበር።
ከሁሉም በላይ እግዚአብሔር ከርሱ ጋር እንደነበር እርሱ ራሱ ህዝቡና ጠላቶቹ ሁሉ ያውቁ ነበር። ከሳዖል በቀር እስራኤል ሁሉ አይኑን የጣለበትና ልቡ ያረፈበት፤ መልከ መልካም እግዚአብሔርን የሚፈራ ጉብል ወጣት ነበር።
ይህ ዳዊት ልቡ ምን ዓይነት ነበር? ዳዊትም ሲናገር እንዲህ አለ፡- “እግዚአብሔር ሆይ፤ ልቤ አልታበየም፤ ዐይኔ ከፍ ከፍ አላለም፤ ሐሳቤ ለዐጒል ትልቅነት አልተነሣሣም፤ ከዐቅሜም በላይ አልተንጠራራሁም። ” (ቁጥር1)
ተመልከቱ ወገኖቼ፤ ልብ በሉ፡- ዳዊት እያናገረ ያለው እግዚአብሄርን ነው። እግዚአብሔር ልብንና ኩላሊትን እንደሚመረምር ያውቃል ፤ ሊዋሽም አይችልም። ዳዊት በዚህ ሁሉ አልታበየም፤ አልተነሳሳም፤ አልተንጠራራምም ነበር።
ስለሆነም እንዲህ እንዳማረበትና እንደተወደደ መንግቱን ከሳዖል እጅ በሰላምና ያለምንም ደም መፋሰስ እንዲረከብ የተመኙ ጥቂቶች አልነበሩም። አልጋ ወራሹን ዮናታንን ጨምሮ። እውነትም ምናለበት ያስብላል!
ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነና በቤተመንግስት ከመኳንንት ጋር በከበረ ስፍራ መቀመጥ ቀረና ፤ የተጨነቁ ፤ ዕዳ ያለባቸውና የተከፉ ሰዎችን እየመራ እንደወንበዴ ዱር ለዱር፤ ከዋሻ ወደ ዋሻ መንከራተቱን ተያያዘው።
ያ ሁሉ አጀብ፤ ያ ሁሉ ክብር ፤ ያ ሁሉ ማዕረግ ፤ ያ ሁሉ ዝናና ሞገስ ቀስ በቀስ ተረሳ።
ዳዊት የደመቀበት ብርሃን ሲደበዝዝ ምን ነበር መልሱ? በብዙዎች መደነቁና መወደዱ፤ መሞገሱና መወደሱ ሲቀርበት ምን ተሰምቶት ይሆን? ያ ልቡን ያሞቅ የነበረው በካሴት አስቀርፆ ያላስቀረው አሞጋሽ የሴቶች ዘፈን የሩቅ ትዝታ ሲሆንበት እንዴት ቻለው ? ይሄኔ ነው እውነተኛው የልብ ባህሪይ የሚገለፀው። እውነተኛ ባህሪያችንና መልካች ሚገለፀው ዙሪያችንን ያደመቀው ብርሃን ሲደበዝዝ ነው። በአገልግሎታችን፤ በሥራችን፤ በቤተሰባችን፤ በግኑኝነቶቻችን ደምቀው የበሩ እኛም የደመቅንባቸው ምስክርነቶቻችን፤ የሰውን ትኩረት የሳብንባቸው ታለንቶቻችን ፤ እንዲታዩልንና እንዲታወቁልን የምንፈልጋቸው ነገሮች ላይ የበራው ብርሃን ድንገት ቢደበዝዝብን ምን ይሆን ምላሻችን? በሰዎች ዘንድ ተፈላጊነታችን ሲቀንስ፤ ሲያወደሱን፤ ሲያሞካሹን የነበሩ ወዳጆቻችን ገሽሽ ገሸሽ ሲሉ ምን ይሆን ነፍሳችንን የሚያረጋጋት? አገልጋዮች የሆን ደግሞ የለመድነው የአደባባይ ብርሃን (public spotlight) ሲደበዝዝ፤ ክርስቶስ አሁንም በውበቱ ይታይብን ይሆን?
ስናጣቸው ብቻ መኖራቸውን የምናስታውሳቸው አሁን ግን የሚጠቅሙንና የሞቁን ብርሃኖች አቤት ብዛታቸው!
ያለነሱ መኖር ምንችል እስከማይመስለን የምንጠነቀቅላቸው ብርሃኖቻችን ሲደበዝዙ የመኖር ተስፋችን አብሮ ይደበዝዝብን ይሆን? መኖር ያስጠላን ይሆን? ራሳችንን እንጠላ ይሆን? በእድላችን
እንመረር ይሆን? መልሳችንን እንደዳዊት ለእግዚአብሄር እንናገር?
ለትልቅነት ጉዞ ጀምረን (ትልቅነት ችግር የለበትም አጉል ትልቅነት አይሁን እንጂ) ገና ከጅምሩ መብራት ቢጠፋብንስ? ትልማችንና ራዕያችንን ድንገት ቢጨነግፍብን፤ መልካም ግኑኝነት ቢበላሽብን ፤ እጮኝነት ቢፈርስብን፤ ዕቅዳችን ሳይሳካ ቢቀር እንደው ምን ይመስል ይሆን ምላሻችን? ፊታችን ላይ የሚነበበው ወንጌል ይሆን ወይስ ምሬት ?
ዳዊት ያጣቸው ነገሮች ሁሉ መብቶቹ ነበሩ? ይህ ደግሞ የፍትህን ጥያቄ ያስነሳል ።
ከሰማይ የተፈቀደለት ዙፋን እንኳ ቢቀር በንጉስ ገበታ መቀመጥ በሰራው ገድል ያገኘው የከበሬታ ቦታ ነበር። እርሱንም አጣ። ሆኖም ግን ዳዊት አልተበሳጨም፤ አሳይቶ ነሳኝ ብሎ በእግዚአብሔርም ላይ አላማረረም፤ ለበቀል ም አልተነሳሳም። ይልቅ እንደዚህ አደረገ፤ ከራሱ አፍ እንስማ… “ነገር ግን ነፍሴን ጸጥ፣ ዝም አሰኘኋት፤ ጡት የጣለ ልጅ ዐርፎ እናቱ ላይ እንደሚቀመጥ፣ነፍሴ ጡት እንዳስተዉት ሕፃን በውስጤ ጸጥ አለች።” (ቁጥር 2)
አንዳንድ  ህፃናትን  ጡት ማስጣል አዳጋች ይሆናል ፤ አንዳንዴ ትግል ፤ አንዳንዴ ብልሃት ይጠይቃል (አባት ነኝ አይቻለሁ)። በትግልም ሆነ በብልሃት ከጥቂት ቀናት በኋላ ህፃኑ አንድ ነገር ያስተውላል። በቃላትና በንግግር ሳይሆን በደመ ነፍስ የሚገባው ነገር አለ። ወላጅ እናቱ አንዳች የተሻለ ነገር እንዳሰበችለት ያውቃል፤ ያምናታልም። ስለዚህም ይረጋጋል። ዳዊትም ያደረገው ይህንኑ ነው። አምላኩና እረኛው እግዚአብሄር ያሰበለትን ተረድቶ ነፍሱን አረጋጋት፤ ዝምም አሰኛት። ምናልባትም የራሱን መዝሙር (መዝሙር 23ን) ሳይዘምርላት የቀረ አይመስለኝም። ነፍሱን ብዙ ጊዜ እየመለሰለት ስለስሙም በፅድቅ መንገድ የመራው እረኛው አሁንም መንገድ ስቶ እንዳማያስተው ለነፍሱ ነገራት። ነፍሱም አወቀች በውስጡም ፀጥ አለች። አልተናወጠችም።
በእግዚአብሄር ፈቃድ እነሳዖል፤ መብራቶቹን አጠፉበት ። የደመቀበት ብርሃን ደበዘዘ ዳዊት ግን እግዚአብሄርን አንተ “ብርሃኔና መድሃኒቴ (ነህ) የሚያስፈራኝ ማነው?” መዝ26፡1። እንዲሁም በሌላ ስፍራ እንዲህ ይላል: – “እግዚአብሔር ሆይ አንተ መብራቴን ታበራለህ አምላኬ ሆይ ጨለማዬን ብርሃን ታደርገዋለህ። “(መዝ19፡28 )
በእግዚአብሔር ላይ በመተማመን ነፍሱን ካረጋጋ በኋላ እርሱ ራሱ በተረጋጋበትና ባረጋጋዉ በእግዚአብሄር ላይ ተስፋ እንዲያደርጉ ለእስራኤል ሁሉ ጥሪ አደረገ። “እስራኤል ሆይ! ከዛሬ ጀምሮ በእግዚአብሔር ተስፋ አድርግ። “ (ቁጥር 3)
እኛስ ወገኖች ሆይ ተስፋችን በማን ነው? ከሰማይ ሰማያት ክብሩን ትቶ ፤ አምላክ ሆኖ ሳለ ለኔና ለናንተ ራሱን ባዶ ያደረገውን፤ እንደዳዊት መብቱንና ክብሩን ብቻ ሳይሆን ፤ ነፍሱን ስለኛ ያጣውን ኢየሱስን እንመለከት፤ መልካም እረኛ እኔ ነኝ ብሎ ነፍሱን በፈቃዱ ስለኛ ያኖረውን፤ እንደወንጀለኛ ተቆጥሮ ከወንጀለኞች መሃል የተሰቀለውን ክርስቶስን እንመለከት ፤ እርሱ ክብራችን ነውና ። እርሱ ተስፋችን ነው`። መልክ ውበቱን አጥቶ የራሱን መልክ ለሰጠን ጌታ መብቶቻችንን ብቻ ሳይሆን ነፍሳችንን እንኳ ብናጣለት አይበዛበትም። እንደጳውሎስ “ ነገር ግን ይጠቅመኝ የነበረውን ሁሉ አሁን ለክርስቶስ ስል እንደጉድፍ ቆጥረዋለሁ።” (ፊል3፡ 7)
ኦ! ይጠቅሙን የነበሩትን ነገሮች ተገደን ሆነ በፈቃዳችን ስንነጠቅ፤ የዚህ ዓለም ብርሃን በነገሮቻችን ላይ ሲደበዝዝ የፊት መጨማደድ ቀርቶ የክርስቶስ የመልኩ ውበት ለዓለም ይታይልን። ያን ጊዜ ዳዊት ነፍሱን በእግዚአብሄር ካረጋጋ በኋላ ለእስራኤል ሁሉ ጥሪ እንዳደረገ ሁሉ እኛም ወዳ በዓለም ላሉ ጥሪ እናደርጋለን። ያን ጊዜ የህይወት ውሃ ምንጭ ከውስጣችን ይፈልቃል። ደስታችን በጌታ ብቻ እንደሆነ ፤ የሰላማችንና የርካታችን ምንጩ ክርስቶስ እንደሆነ አህዛብ ያስተውላሉ።
ደማቅ ብርሃኖቻችን ሲደበዝዙ በህይወታችን ደምቆ የሚበራልን የክርስቶስ መልክ ይሁንልን።
“የሱስ ካለኝ
ሁሉም አለኝ”

አብርሃም ቀጠና በለው