የማይዋዥቅ ማንነት

የስኬት ደስታ እንደ ወይን ጠጅ ቶሎ ራስ ላይ ይወጣና ሰው መሆናችንን ሊያስረሳን ሲችል ፤ የውድቀት ወይም የአለመሳካት ሃዘን ደግሞ ወደ ልብ ወርዶ ሰው መሆናችንን ሊያስጠላን ይችላል። ሁለቱም ማለትም ስኬትና ውድቀት ህይወታችንን የማመሳቀል አቅማቸውና አደገኛነታቸው እኩል ነው። በምድር ላይ እስካለን ሁለቱም እንድየምክንያቶቻቸው ተራ በተራ ሊፈራረቁብን የግድ ነው ። ስለሆነም ሁለቱንም እንደየአመጣጣቸው ተቋቁመን፤ ሰላማችን ሳይናጋና ነፍሳችንም ሳትታወክ በድል ማለፍ የምንችለው እግዚአብሄር በክርስቶስ ኢየሱስ የሰጠንን ማንነት በትክክል ስንረዳ ብቻ ነው። ንጉስ ዳዊት ከዙፋኑ በተባረረ ጊዜ እንዲህ አለ፦ ” እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ግን ዙሪዬን የምትከልል ጋሻ ነህ: ክብሬና ራሴንም ቀና የምታደርግ አንተ ነህ።” (መዝ 2፡3) እግዚአብሔርን ” አንተ ክብሬ ነህ” አለው። ደቀመዛሙርት አገልግሎት ተሳክቶላቸው፤ አጋንንት በስሙ ሲገዙላቸው አይተው ሲደሰቱ፤ ጌታ ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፦” … መናፍስት ስለተገዙላችሁ በዚያ ደስ አይበላችሁ፤ ስማችሁ በሰማይ ስለተፃፈ ደስ ይበላችሁ።” (ሉቃ10፡20)
እግዚአብሔር በክርስቶስ የሰጠን ማንነት በመሳካት ወይም ባለመሳካት የሚዋዥቅ አይደለም። ስለዝህ በስኬት ከፍታ አንመካ ይልቅ ስማችን በሰማይ በመፃፉ እንጂ ፤እንዲሁም በዝቅታችንም ራሳችንን እየጠላን ከመማረር ይልቅ እንደ ዳዊት እግዚአብሄር በክርስቶስ ኢየሱስ ክብራችን ስለሆነ ደስ ሊለን ይገባል። ” ዝቅ ያለው ወንድም ከፍ በማለቱ ይመካ። ባለጠጋውም ዝቅ በማለቱ ይመካ፤ እንደሣር አበባ ይረግፋልና።” (ያዕ 1፡9,10.)
ኢየሱስ ሁሉን ለዘላለም እኩል አድርጓል ። ሁሉም በክርስቶስ ለዘላለም እኩል ሆኗል። ለርሱ ከዘለም እስከዘላለም ክብር ይሁን። አሜን።

Leave a Reply