ከምሪት ይልቅ መሪውን

ከምሪት ይልቅ መሪውን

በጉዞ ላይ ያለ መንገደኛ ካሰበበት ገና ሳይደርስ ፀሃይ ብታሽቆለቁል ድንግዝግዝታ ይሆንበትና ጉዞውን ለመቀጠል ይቸገራል። የቀረውን ርቀት ከቀረው አቅምና ሰአት ጋር በሃሳቡ እያነፃፀረ፤ ሳይጨልም እደርስ አልደርስ እያለ በልቡ ማመንታት ይጀምራል።እንዳይቀጥል ከፊቱ ለፊቱ የሚጠብቀው ጨለማና የጨለማ መዘዞች ያስፈሩታል። እንዳይቆምና ገና አልመሸም ፤ ባለበትም እንዳያድር ማደሪያ የለም። በዚህ ሁኔታ እያለ ሳያስበው የእርምጃውም ፍጥነት ይቀንሳል። በድንግዝግዝታ ውስጥ መሄድ ሆነ መቆምም ያስቸግራል። እንዳይሄድ ብርሃን አይደለም እንዳይቆምም ጨለማ አይደለም። ለውሳኔ ወይም ለምርጫ የሚያስቸግርና የሚያዳግት ፤ ግራ የሚገባ ጊዜና ሁኔታ ነው።
አንዳንድ ጊዜ የክርስቲያን ህይወት እንዲህ ድንግዝግዝ ባለ ሁኔታ ወይም ጊዜ ውስጥ ታልፋለች። ይሁን እንጂ ህይወቱ ፈፅሞ ያለእረኛ(መሪ) አይደለችም። እረኛውም “ራስህ ተወጣው” ብሎ አማኙን ለራሱ ማስተዋል ፈፅሞ አይተወውም። አማኝም በድንግዝግዝታ ጊዜ ሆነ በሌላ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ በራሱ ማስተዋል መደገፍ ከቶውን የለበትም። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ አማኝ ያለበትን ግራ የሚገባ ሁኔታ የሚያስረዳ መረጃ ሆነ ካለበት ሁኔታ ውስጥ የሚወጣበትን ምሪትና ጊዜውን ማወቅ ምን ያህል እንደሚፈልግ እረኛው ቢያውቅም የሚሻለውን እንዲፈልግ ፈልጎ ዝም ይለዋል። አማኝም ከእረኛው ዝምታ የተነሳ ከመደናገጥና(panic) በችኮላ የራሱን ዜዴ ከመዘየድ ተቆጥቦ፤ ድንግዝግዝታው አማኙን ወደራሱ የበለጠ ለማቅረብ በእረኛው አስቀድሞ ታውቆ የታቀደ እንጂ ድንገተኛ ሁኔታ ወይም ጊዜ አለመሆኑን አስተውሎ ከምሪት ይልቅ መሪውን መፈለግ እጅጉን ይበጀዋል።
በብዙ ነገሮች ግራ የተጋባን፤ መሄድ ወይም መቆም ያልቻልን ፤ አጥርተን ማየት ያልቻልንና በአንዳንድ ጉዳዩቻችን ድንግዝግዝታ ውስጥ ያለንና መወሰን ያቃተን ሁላችን፦ እስቲ ምሪት ትተን መሪውን እንፈልግ።
እግዚአብሄር አምላክ ለጠየቀው ወይም ላስፈለገው ሁሉ በመረጃ ደስክ ላይ ተቀምጦ መረጃ የሚሰጥ ሰራተኛ ወይም እንደ ጉግል(Google) የኢንፎርሜሽን ውቅያኖስም አይደለም። እግዚአብሔርን እንደዚህ(እንደ ጉጉልና እንደ መረጃ ሰጪ ሰራተኛ) እንደምናውቀው የማናውቅ ጥቂት አይደለንም። ይህንንም ለማረጋገጥ የፀሎት ህይወታችንን ማየት ብቻ በቂ ይመስለኛል። ለፀሎት የምንነሳሳው መቼ ነው? እግዚአብሄርን ስንፈልግ ወይስ ከእግዚአብሄር ስንፈልግ?
እግዚአብሄር መፈለግን ይፈልጋል። እግዚአብሔር የአንተ የግል እረኛህ፣ የአንቺ የግል እረኛሽ፣ የኔ የግል እረኛዬ ነው። የኔ የግሌ፣ በግል የማውቀው፣ በግል የሚያውቀኝና በፍቅር የተሳሰርን ፣ የራሴ የምለው እረኛዬ መሆኑን እንዳውቅ ይፈልጋል። በግል መታወቅም ይፈልጋል።
“እግዚአብሄር እረኛዬ ነው፤ የሚያሳጣኝም የለም።” (መዝ23:1) እግዚአብሄር እረኛችን ሰለሆነ ከማያሳጣን ነገሮች አንዱ ምሪት ነው። ሰለዚህ ከምሪት ይልቅ ምሪትን ጨምሮ መልካም የሆነውን ሁሉ የማያሳጣንን እረኛችንን በግል እንወቀው።
(በለመለመ መስክ ያሳድረኛል በእረፍት ውሃም ዘንድ ይ መራኛል።)
አንድ ነገር እርግጠኞች እንሁን፦ እረኛችን ለመለመ መስክ ያሳድራል፤ ወደእረፍት ውሀም ይመራናል በሞት ጥላ መካከል ስናልፍ ግን ከእኛ ጋር ይሆናል። እንዳንፈራ የሚያደርገን የእረኛችን ምሪቱ ሳይሆን አብሮነቱ ነው። ምናልባት አሰልቺው የድንግዝግዝ ኑሮአችን ሞትን የሚያስመኝ የህይወት ፈተና ሆኖብን ሊሆን ይችላል። ታዲያ በዚህ ሞትን በሚያስመኝ ሁኔታ ውስጥ ስናልፍ እንኳ ከምንም በላይ የሚያስፈልገን ምሪት ሳይሆን እረኛው እራሱ ነው። በሞት ጥላ መካከል እንደዳዊት በርግጠኝነት” አንተ ከኔ ጋር ነህና” ለማለት እረኛውን በደንብ ማወቅ ይጠይቃል። ሰለዚህ ማናቸውም ዓይነት የድንግዝግዝታ ጊዜያችን ወይም ሁኔታችን ከምሪት ይልቅ መሪውን የምናውቅበት ገዜ እንዲሆንልን ፀጋው ይደግፈን።እረኛችን ከሚሰጠን ምሪት ይልቅ ራሱን መስጠት ይወዳል።
ያዳነንም ራሱን ሰጥቶን ነው።

አብርሃም ቀጠና በለው

Leave a Reply